በአርባምንጭ ከተማ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአርባምንጭ ከተማ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል
አርባምንጭ፤ ጥቅምት18/2018(ኢዜአ)፡-በአርባምንጭ ከተማ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ የሚያስችል አሰራር በየደረጃው መዘርጋቱን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
በከተማው አስተዳደር የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያቀላጥፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የአንድ መስኮት አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል።
አገልግሎቱን ያስጀመሩት የከተማው አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ናቸው።
ከንቲባው፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ለማቀላጠፍ በከተማው በሁሉም ቀበሌዎች የአንድ መስኮት አገልግሎት በሰው ሀይልና በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መደራጀቱን ተናግረዋል።
በከተማው በሁሉም ቀበሌዎች የተመቻቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት የአስተዳደር ፣የንግድ ፣የገቢ ፣የማዘጋጃ ፣የፖሊስና ሌሎች ተቋማትን ያቀፈ በመሆኑ እንግልትንና የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል እንደሆነ ከንቲባው አብራርተዋል።
ከአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጩባ ጭኖ በሰጡት አስተያየት፤ አስተዳደሩ ከተማውን የሚመጥንና ሁሉንም ተደራሽ ያደረገ የተቋማት አገልግሎት ማመቻቸቱ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ይገጥማቸው ከነበረው እንግልትና የጊዜ ብክነት በመላቀቅ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ከወረቀት ነፃ የሆነ አሰራር መመቻቸቱ መልካም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ አንዳርጌ ናቸው።