የኒኩሌር ፕላንት ፕሮጀክት የሕክምና አገልግሎትን ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኒኩሌር ፕላንት ፕሮጀክት የሕክምና አገልግሎትን ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድጋል
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ የኒኩሌር ፕላንት ፕሮጀክት የሕክምና አገልግሎትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
በቅርቡ ይፋ የተደረገው የኒኩሌር ፕላንት ፕሮጀክት ከሀይል አማራጭነት የዘለለ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ከእነዚህ ጠቀሜታዎች መካከል አንዱ የኒኩሌር ህክምና አገልግሎት ይገኝበታል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር፣ ሀኪም፣ ተመራማሪና የካንሰር ሕክምና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ሁነኛው ለኢዜአ እንደገለፁት የኒኩሌር ፕላንቱ በሕክምናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው።
በተለይ በዋናነት የካንሰር በሽታን ለማከም ያለው ፋይዳ ላቅ ያለ በመሆኑ የህክምና አገልግሎቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሰዋል ብለዋል።
አክለውም ለራዲዮ ቴራፒ ሕክምና የሚውሉ መድሀኒቶችን ለማምረትና የቆይታ ጊዜያቸው ከስምንት ቀን የማይበልጡ መድሀኒቶችን ብልሽት መፍታት ያስችላል ነው ያሉት።
ከኒኩሌር ጋር በተያያዘ መንግስት የወሰደው ኢንሼቲቭ ከህክምና አገልግሎቱ ባለፈ በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያለው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ መበረታታት እንዳለበት ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው መምህርና የህጻናት ካንሰር ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ሙሉአለም ንጉሴ በበኩላቸው ያደጉ ሀገሮች የኒኩሌር ሕክምናን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቀሙበት አንስተዋል።
የኒኩሌር ሀይል ለአዋቂም ሆነ ለሕጻናት ሕክምና የበሽታውን ሁኔታና ያለበትን ደረጃ ለይቶ ለማከም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ለሕክምናው ዘርፍ ጭምር ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል።
የኒኩሌር ሀይል ለካንሰር ሕክምና አገልግሎት ሦስት ዋና ዋና ፋይዳ አለው ያሉት ባለሙያው የካንሰር አይነቱንና የስርጭቱን መጠን እንዲያውቅ ይረዳዋል ነው ያሉት።
ሕመምተኛውም የበሽታው አይነትና ስርጭትን መሰረት ያደረገ ሕክምና እንዲያገኝ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።
ለካንሰር ሕሙማን የኒኩሌር ሕክምና በሀገር ውስጥ ስለማይሰጥ ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ውጪ እንደሚላኩ የገለጹት ዶክተር ሙሉአለም በዚህም ምክንያት ለወጪና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኒኩሌር ሕክምና ከሌሎቹ የሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ እና ሌሎች መሳሪያዎች አንጻር ያለውን በሽታ ለይቶ ማሳየት ብቻ ሳይሆን ያደረሰውን የጉዳት መጠን ጭምር ለይቶ የሚያሳይ ነው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ክብሩ ክፍሌ ናቸው።
በካንሰር የተጠቃ የሰውነት አካል ምን ያህል እንደተጎዳ፣ የትኛው ክፍሉ ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ እንደሚገኝ የሚለውን በትክክል መለየት የሚያስችል የዘመናዊ ሕክምና ትልቅ መሳሪያ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሀገር ይፋ የተደረገው የኒኩሌር ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያሸጋግር በመሆኑ መንግስት የወሰደው ተነሳሽነት ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል ሲሉም ምሁራኑ ገልፀዋል።