ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ የበኩላችንን እየተወጣን ነው - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰላማዊ፣ በሰጥቶ መቀበልና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል።
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን እንድታጣ ያደረገውን ውሳኔ ማን ወሰነ ብለን ስንፈልግ ተቋማት አልገቡበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ተዘግቶባት መኖር አትችልም ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የምክር ቤት አባል አቶ ሳዲቅ አደም እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍና በተለያዩ ኮንቬንሽኖች ተቀባይነት ያለው ነው ።
ኢትዮጵያ ከባህር በር ርቃ የቆየችበት መንገድ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ጥያቄ የሰጥቶ መቀበል መርህን እና ሰላማዊ መንገድን ያስቀደመ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበው፤ ምክር ቤቱም አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባል አስቴር ከፍታው በበኩላቸው፤ የባህር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ መሆን የምትፈልገው በሰላማዊ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ስኬት የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ መላው ሕዝብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ የባህር በር ይህንኑ ፍላጎት ለማሳካት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤት አባል አምባሳደር ተውፊቅ አብዱላሂ (ዲ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የመላው ሕዝብ አጀንዳ መሆኑን ተናግረው፣ አጀንዳው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተመሰረት መሆኑን ጠቁመው፤ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት አለበት ብለዋል።
ፍትሐዊ የሆነው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።