ቀጥታ፡

በየተቋማችን የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ እንተጋለን  - የመንግስት ሠራተኞች

ጎንደር/  ገንዳ ውሃ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፡- በሰላም ግንባታ ላይ  ተሳትፏቸውን  በማጎልበት  በየተቋማቸው  የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰሩ  በጎንደር ከተማ የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ።    

 ሠራተኞቹ "የውጭ ባንዳዎችንና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዠት በማምከን አንፀባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን " በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ሠራተኞቹ እንዳሉት፤ አገልግሎት አሠጣጥን በማዘመን ቀልጣፋና ፈጣን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሰራሉ።    


 

ከተሳታፊዎቹ መካከል አስካል ፀሐይ በሰጡት አስተያየት፤ የመንግስት ተቋማትን የአገልግሎት አሠጣጥ ለማዘመን የተጀመሩ የዲጂታል  ቴክኖሎጂ  አሰራሮች የተገልጋዩን እንግልትና ቅሬታ የሚፈታ መሆኑን አንስተዋል።  

ይህም  የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ከመሰረቱ የሚፈታና ሠራተኛውም በተመደበበት መስክ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ የስራ ምህዳር የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛው ተሳታፊ መልካሙ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሠራተኛውን የስራ ተነሳሽነት የሚያጎለብትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እውቀቱንም ከፍ የሚያደርግ  መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በተመረጡ ተቋማት የጀመራቸው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ሁሉም ተቋማት እንዲሠፉ የሚደግፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂው  የተገልጋዩን  ጊዜ  ፣ገንዘብንና ጉልበትን ቆጥቦ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ አቶ ባዘዘው ታምራት ናቸው፡፡

ሠራተኞቹ  በሰላም ግንባታ ላይ ሲያደርጉ የቆዩትን   ተሳትፎ  በማጎልበት  በየተቋማቸው  የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ በታማኝነትና በቅንነት ተግተው  እንደሚሰሩ ገልጸዋል።     

የጎንደር ከተማ አስተዳደር  ሲቪል ሲርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ነጻነት መንግስቴ  እንደገለጹት፤ መሶብ የአንድ ማዕከልን  ጨምሮ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ   አገልግሎት አሰጣጥ  ቀልጣፋና ፈጣን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡


 

በመንግስት ለሠራተኛው የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ  የስራ ተነሳሽነቱን የሚያጎለብት በመሆኑ ሠራተኛው በሠላም ግንባታና በልማት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ የምዕራብ ጎንደር ዞን  የመንግስት ሠራተኞች  ውይይት አካሄደዋል። 


 

በገንዳውሃ በተካሄደው ውይይት  ከተሳተፉት ሠራተኞች መካከል  ዮሐንስ ዓለሙ  የውጭና የውስጥ ጠላቶችን ሴራ በአንድነት በማክሸፍ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  ተናግረዋል።

ሌላው ተሳታፊ ግርማ ሰፊው ፤ ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር አፍራሽ አጀንዳዎችን ቀድሞ በመገንዘብ ለመመከት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። 

በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር  የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ አትጠገብ አሻግሬ ናቸው።


 

የዞኑ ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ቢተው አሳየ በበኩላቸው፤  ነጠላ ትርክትን በማስወገድ ሀገሪቱ የያዘችውን የእድገት ጎዳና ማስቀጠልና ሰላምን ማፅናት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።  

የመንግሥት ሠራተኛው ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት የሕብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም