ከአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 170 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
ከአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 170 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ታቅዷል
ባህርዳር ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ከአማራ ክልል በያዝነው ዓመት 170 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሆልቲካልቸር ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የቡና ልማትን በማስፋፋትና ምርታማነቱን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ በስነ ምህዳርና በአየር ንብረታቸው ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች በኩታ ገጠም ጭምር ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቡና ልማት እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ውስጥም ምርት መስጠት ከጀመረው 25 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 170 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ቡና በማምረት ለአካባቢና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የለቀማና ምርት ስብስባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ለአምራች አርሶ አደሮች ስለቡና ምርት አሰባሰብ፣ አደራረቅና አዘገጃጀት ግንዛቤ በመፍጠር ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢጠህናን ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ውበት ተስፌ ግማሽ ሄክታር በሚጠጋ መሬታቸው ላይ የተሻሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ዝርያ እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ ለማቅረብ የደረሰውን ምርት እየለቀሙ በአልጋ ላይ በማድረቅ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሻሻለ የቡና ዝርያ በሩብ ሄክታር መሬታቸው ላይ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የዳንግላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላቱ እንግዳ ናቸው።
ዘንድሮ ወቅቱ ለቡና ልማት ተስማሚ በመሆኑ የተሻለ የቡና ምርት በመሰብሰብና በመሸጥ ከሰብል ልማቱ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት 130 ሺህ ኩንታል ቡና ለገበያ መቅረቡን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።