ቀጥታ፡

በተደረገልን አቀባበል ተደስተናል-አዲስ ገቢ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች

ሮቤ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፡- በዩኒቨርሲቲው እና በአካባቢው ማህበረሰብ የተደረገልን አቀባበል በትምህርታችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን ፈጥሮልናል ሲሉ በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው 2 ሺህ 592 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እየተቀበለ ይገኛል።


 

አዲስ ገቢ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማህበረሰብ የተደረገላቸው አቀባበል በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። 

አቀባበል ከተደረገላቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ከሰሜን ሸዋ ዞን የመጣችው ቤተልሄም ቦጋለ በሰጠችው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸው አቀባበል ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራለች። 


 

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም ትኩረቷን በትምህርት ላይ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደምትተጋ ገልጻለች።

የተደረገላቸው አቀባበል በትምህርት ቆይታቸው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን እንደሚፈጥር የገለጸው ደግሞ ከምዕራብ አርሲ ዞን የመጣው ተማሪ ሙዘይን አቡ ነው።


 

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ረመዳን ሉቅማን በበኩሉ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት አባላትና በጎ ፈቃደኛ ነባር ተማሪዎች በማቀናጀት ለአንደኛ ዓመት ተማሪዎቹ አቀባበል እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል።


 

የዩኒቨርሲቲው ዋና ሬጂስትራር ዳይሬክተር አብዱልሀይ አብደላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የተመደቡለትን 2 ሺህ 592 የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን  እየተቀበለ ነው። 


 

ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የመኝታ፣ የመማሪያና የመመገቢያ ክፍሎች  እንዲሁም የመማርያ ቁሳቁስ ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል። 

አዲስ የተቀበላቸውን ጨምሮ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያስተማረ መሆኑም ተመልክቷል።

በቅበላ መርሐ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችን ጨምሮ የተማሪዎች ህብረት አባላት፣ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም