የአርባ ምንጭ ስታዲየም ግንባታን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭ ስታዲየም ግንባታን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ነው
አርባምንጭ ፤ ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ስታዲየም ግንባታን በሕብረተሰቡ ተሳትፎ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ለስታዲየሙ ግንባታ ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ እየተገነባ ያለው የአርባምንጭ ስታዲየም ለዞኑ፣ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት የበኩሉን አሰተዋጽኦ ይኖረዋል።
በአካባቢው ለእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ስፖርተኞች እንዳሉ አውስተዋል።
ስታዲየሙ ግንባታው 30 በመቶ መድረሱን ጠቁመው ለሀገር ተተኪና ተወዳዳሪ ስፖርተኞች ለማፍራት የሚደረጉ ጥረቶች ዕውን እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።
የስታዲየሙን ግንባታ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ሕዝቡን የሚያሳትፍ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች መመቻቸታቸውን አስረድተዋል።
ከእነዚህ መካከልም በቴሌ አጭር መልዕክትና ቶምቦላ ሎተሪ ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በትልቅ አስበን በትልቅ ጀምረናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ለጋራ የሆነው ፕሮጀክት በተባለለት ጊዜ እንዲጠናቀቁ በየደረጃው የሚገኘው ሕብረተሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕከት አስተላልፈዋል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአርባምንጭ ስታዲየም በሕዝብና በመንግስት ትብብር የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የ33 ወራት ውል ተገብቶ እየተከናወነ የሚገኘው የስታዲየሙ ግንባታ በአንድ ዓመት ቆይታ ሂደት 30 በመቶ ደረጃ መድረሱን አስታውቀዋል።
የስታዲየሙ ግንባታ ከአካባቢው አልፎ የሀገር ፕሮጀክት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ ድጋፋቸውን እየገለጹ መሆኑን አንስተዋል።
በቻይና ኮሙኒኬሽን እና ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ተቋራጭነት እየተገነባ ያለው የአርባ ምንጭ ስታዲየም 25 ሺህ ሰዎችን የሚይዝና የመሮጫ ትራክን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶችን ማስተናገድ የሚችል ስፍራ እንደሚኖረው ተመላክቷል።