በሐረሪ ክልል የሰላምና ልማት ስራዎችን የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የሰላምና ልማት ስራዎችን የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሐረር ፤ ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የሰላምና ልማት ስራዎችን የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በትኩረት ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ለክልሉ አመራር አባላት አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በወቅቱም ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሰላምና ልማት ስራዎችን የማረጋገጥ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ህገወጥ የመሬት ወረራና የቤት ግንባታ እንዲሁም ህገ ወጥ ንግድን የመከላከሉና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር በአመራሩ በትኩረት ሊከናወኑ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት የተጀመሩና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት የማብቃት ስራ ላይ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እንዲሁም በኮሪደር ልማት የተጀመሩ ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ የማጠናቀቅ ስራን ማከናወን ይገባል ሲሉም አክለዋል።
በበጀት ዓመቱ አዲስ በዕቅድ የተያዙ የወንዝ ዳርቻ ልማትና ሌሎች ስራዎችን በፍጥነት ወደ ስራ የማስገባት ተግባር ይከናወናል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የገጠሩን ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ በምርት አሰባሰብ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይከሰት በማድረግ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ እስኪያቀርብ ድረስ ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ሲሉም አክለዋል።
በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት የመስጠት ስራን ማሳለጥ እንደሚገባም አመልክተዋል።