ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን የሚያሻሽሉና ትውልድን የሚገነቡ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን የሚያሻሽሉና ትውልድን የሚገነቡ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዛሬ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንድገለጹት፤ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ትውልድን የሚገነቡና የሚያንጹ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ከእነዚህ መካከልም በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚገኙ አዋኪ ድርጊቶችን የማጥራት እንዲሁም በትምህርት ለትውልድ ፕሮጀክት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ለመምህራን የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ከመስጠት ባሻገር በትምህርትና በፈተና አሰጣጥ ላይ ለውጥ እንዲመጣ መደረጉን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤት አካባቢዎችም የስፖርት ማዘውተሪያና የመዝናኛ ስፍራዎችን በመገንባት ጤናማ ትውልድ መገንባት መጀመሩን ነው የተናገሩት።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ከ43 ሚሊየን በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ መጻሕፍት መታደሉንና ይህም የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ከተሰሩ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀዋል።

የተማሪዎች ምገባን በተመለከተም አስደናቂና ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች በመስራት ሁሉም የሚመኛት ኢትዮጵያ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም