ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሁሉም በረከትን ይዞ የመጣ ታላቅ ዕድል ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሁሉም በረከትን ይዞ የመጣ ታላቅ ዕድል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ሁሉም ሀገር በተፈጥሮ ጸጋው ሌላውን ሳይጎዳ የመጠቀም መብት አለው ብለዋል፡፡

ሁሉም አገር ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች እንዳሉት ገልጸው እነዚህም ብሄራዊ ጥቅምና የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶች ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህን ስጋቶች ባለው መረጃ ልክ እንደሚወሰኑ ጠቅሰው፤ ሀገራት በመረጃ እጦት ወይም መሳሳት ብሄራዊ ጥቅምን በተገቢው መንገድ ሊተረጉሙት አይችሉም ብለዋል፡፡

የሰው ልጅ ፍትህን ለማረጋገጥ መትጋት እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ ባለበት ዓለም ላይ የተሟላ ሰላም ሊፈጠር አይችልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሄራዊ ጥቅሟ ላይ ኢ-ፍትሃዊ በደል ደርሶባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቢያንስ ይህንን መናገር አትከልክሉን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ተጠቀመችበት እንጂ ማንን ጎዳች፣ ኢነርጂ አመረተች እንጂ መች ውሃ ከለከለች፣ እኛ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት መጠቀም እንጂ ማንንም መጉዳት አንፈልግም ብለዋል፡፡

ውሃው ጨመረ እንጂ መች ቀነሰ፣ ሳንጠቀም ድርቅ ነበር ፣አሁን ግድቡን ባንገድበው ኖሮ የጎርፉ ስጋት ምን ያመጣ ነበር ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ግብጻውያንና ሱዳናውያን ወንድሞቻችን ናቸው፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠረና በብዙ መልኩ የተጋመድን ህዝቦች በመሆናችን ከኢትዮጵያ ልማት መጠቀም ነው እንጂ ኢትዮጵያ እንዳትለማ መከልከል ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ሶስቱ ሀገራት ህዝባቸውን በማስተባበር በጋራ በመስራት ለአፍሪካውያን መትረፍ እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሁሉም በረከትን ይዞ የመጣ ታላቅ ዕድል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን ማንም ሃይሉን በጉልበት ሊጭንብን አይችልም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም