የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ እንደሆነ እናምናለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምና ጸጥታን በሚመለከት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊ (ጂኦግራፊያዊ)፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ እንደሆነ እናምናለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለማጣት 30 ዓመት በላይ የወሰደ ትግል እንደነበር ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቷ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ 30 ዓመት አያስፈልጋትም ብለዋል።
ይህን ጉዳይ ለመፍታት በተረጋጋ፣ በሰከነ እና በውይይት መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ "ለማጣት የፈጀውን ያህል ለመመለስ አይፈጅብንም" ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልወሰነው፣ ተወካዮች ያላዩትና ካቢኔም ያልወሰነው ውሳኔ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ትልቅ ጉዳይ ማን ወሰነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት መንገድ ህጋዊ እና ተቋማዊ መሠረት የሌለው ነው ብለዋል።