ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ጥረት እንደግፋለን-የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ጥረት እንደግፋለን-የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን ተከትላ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ በቁርጠኝነት እንደሚደግፉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትጠቀመው የቆየው የባህር በር በታሪክ አጋጣሚ ከእጇ ወጥቶ ከወደብ አልባ ሀገራት ተርታ ተሰልፋ ቆይታለች።
መንግስትም የኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ሆኖ የቆየውን የባህር በር ጥያቄ በይፋ በማንሳት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።
ይህንንም የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር አጽንኦት መስጠታቸው የሚታወስ ነው።
በጉዳዩ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የባህር በር ጥያቄው የትውልዱ የዘመናት ቁጭትን የሚመልስ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መንግስት የጀመረው ጥረት እንዲሳካ በቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ የባህር በር ለሀገር ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት መሰረት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህግን በተከተለና ዲፕሎማሲየዊ በሆነ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት እንዲሳካም ምክር ቤቱ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትጠቀምበት የነበረውን የባህር በር ማጣቷ ለድህነታችን አንድ ምክንያት ከመሆኑ በላይ የሚያስቆጭ ነው" ያሉት ደግሞ የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ ተፈራ ጎበና ናቸው።
የባህር በር ጥያቄን ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶችን ማጠናከር ለድርድር መቅረብ የለበትም ያሉት አቶ ተፈራ የጉዳዩ መሳካት ልማትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማፋጠን አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የባህር በር ለማግኘት መንግስት የጀመረው ተግባር ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እውን እንዲሆን ፓርቲያቸው የሚጠበቅበትን ይወጣል ሲሉም ገልጸዋል።
የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሚልክያስ ሳንታ በበኩላቸው መንግስት የባህር በር ለማግኘት የጀመረው ተግባር ወቅቱን የጠበቀ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በታሪክም ይሁን በህግ ተገቢነት እንዳለው አንስተው ጉዳዩም የትውልዱ ጭምር መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት ለኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልግ በይፋ መናገር ከጀመረ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃም አጀንዳ እየሆነ መምጣቱ ጥሩ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለስኬታማነቱም በተለይ የኢትዮጵያ አጎራባች ሀገራት ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
የባህር በር መኖር ሀገሪቱ አሁን እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ዕድገት አጠናክሮ የማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አቶ ሚልክያስ አንስተዋል።
በመሆኑም ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በግልም ሆነ እንደ ፓርቲ ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።