የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ)፦ የ2018 የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ ረፋድ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን አግኝቷል።
በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ ቡራዩ ክፍለ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በተመሳሳይ በጅማ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሱሉልታ ክፍለ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ውጤቶቹን ተከትሎ ጋሞ ጨንቻ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።
መርሃ ግብሩ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል ባቱ ከተማ ከቤንች ማጂ ቡና በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሃላባ ከተማ በጅማ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር እስከ ነገ ይቆያል።
በመጀመሪያው ዙር ውድድር የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ብቻ የሚሳተፉ ሲሆን አሸናፊ ቡድኖች በሁለተኛው ዙር ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ጋር በመቀላቀል እንደሚጫወቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ወላይታ ድቻ የወቅቱ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ ነው።
የኢትዮጵያ ዋንጫ የሚያሸንፍ ቡድን በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።