ቀጥታ፡

በዚህ ዓመት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን 100 ለማድረስ እየተሰራ ነው-  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦በዚህ ዓመት የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን 100 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት አባላት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ላነሱላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፥ በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ  ላይ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 

ባለፈው ዓመት  መሶብ  የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን አንስተው፤  በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን  ቁጥር  18  ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በቅርቡም ሦስት የአገልግሎት ማዕከላት ወደ ስራ እንደሚገቡ በመጠቆም፥ በተያዘው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ  መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጣቢያዎችን 100 ለማድረስ እየሰራን ነው ብለዋል።

የመሬት፣ ግብር፣ የንግድ ፈቃድ፣ ፓስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን በማሻሻል ረገድ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል። 

የዜግነትና ኢሚግሬሽን አገልግሎት ላይ የተሰራው ሪፎረም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን  የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከሶስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ፓስፖርት የመስጠት አቅሟ  270 ሺህ  እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ በዓመት 4 ሚሊየን ፓስፖርት የማቅረብ አቅም ተፈጥሯል ብለዋል። 

ይህም ውጤት የተገኘው በተቋማዊ ሪፎርሙ ስር ነቀል ለውጥ በመደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም