ቀጥታ፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ ይሆናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሔደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ሲሆን በማብራሪያቸው፤ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ምርጫው አማራጭ ድምጾች ይበልጥ የሚካተቱበት እንደሚሆን ይጠበቃል ነው ያሉት።

ለዚህም እንደ መንግስት እና ፓርቲ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠው፤ ይህን ለማስፈጸም በቂ አቅም እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡

ምርጫውን ለማከናወን መንግስት በቂ አቅምና ዝግጁነት አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን በኢትዮጵያ ከተካሄዱ ምርጫዎች የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ብለዋል።

ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ብዘሃ ድምጾች ያሉት እንዲሆን በሃላፊነት እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።

እኛ እንደ ፓርቲም፤ እንደ መንግስትም ዝግጁ ነን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።

በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም