መንግሥት ወደ ሰላም ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ጋር አብሮ ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ወደ ሰላም ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ጋር አብሮ ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦መንግሥት ወደ ሰላም ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ጋር ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመስራት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምና ጸጥታን በሚመለከት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የሰላምና የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ መንግሥት ሰላምን ቀዳሚ አማራጭ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን በሁለት እግር መቆም የማይፈልጉ ሀገራት በጦርነት ሊያሸንፉን እንደማይችሉ በደንብ ስለሚያውቁ ያላቸው አማራጭ ተላላኪ ባንዳዎችን መላክ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን እገነጥላለሁ ወይም እጠቀልላለሁ የሚል ኃይል የኢትዮጵያን ባህል በቅጡ ባለማወቅ የፈጠረው ህልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸረ ሰላም ኃይሎች ቀላል መንገድ የሚመስላቸው ከጠላት ጋር ማበር ነው ብለዋል።
ይሄ ችግር ባለበት የተሟላ ሰላም ማምጣት የራሱ ችግር እንዳለበትም አስረድተው፥ ሰላም ትዕግስትና ጊዜ እንደሚፈልግ ጠቅሰዋል።
ነፍጥ ካነሱ ወገኖች ጋር በመወያየት በሰላም ስልጣን የያዙና ከመንግሥት ጋር አብረው እየሰሩ የሚገኙ መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ፍላጎት እስከ ተግባባን ድረስ የግል ጉዳይን መተው አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ከሚመጣ የትኛውም ኃይል ለመነጋገርና ለመታረቅ ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመሥራት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
አሁንም ለሰላም በራችን ክፍት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ካልተደመርንና ካልተጋገዝን የኢትዮጵያን ችግሮች በአጠረ ጊዜ ልንፈታ እንደማንችል በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ አብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።