ቀጥታ፡

አካታች ሀገራዊ ምክክር ነባር ችግሮችን በመፍታት መፍትሄ ያመጣል 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦አካታች ሀገራዊ ምክክር ነባር ችግሮችን ለመፍታት መፍትሄ ያመጣል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሔደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ በኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋል፤ የእርስ በእርስ ግጭቶችም መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን እድገት የማይወዱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪዎችን በመጠቀም ውስጣዊ ሰላማችንን እያወኩ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህ ተላላኪዎች የታሪካዊ ጠላቶቻችንን  አጀንዳ ተሸክመው ከማወክ የዘለለ የሚያሳኩት አጀንዳ ሆነ የሚሳካ እቅድ የላቸውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን መጠቅለልም ሆነ መገንጠል አይቻልም ይህን የሚያስቡ ኢትዮጵያን በትክክል የማያውቁ ናቸው ብለዋል፡፡

መንግስት ለሰላማዊ ትግል ያለው ቁርጠኝነት የማይናወጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም አካታች ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ነባር ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔ ያመጣል ብለዋል።

ለሃሳብ ፖለቲካ አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም