ቀጥታ፡

የወጣቶችን የእግር ኳስ ፍላጎት የሚጨምሩ ከ1 ሺህ በላይ አነስተኛ መጫወቻ ሜዳዎች በአዲስ አበባ ተገንብተዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ)፡-የወጣቶችን የእግር ኳስ ፍላጎት የሚጨምሩ ከ1 ሺህ በላይ አነስተኛ መጫወቻ ሜዳዎች በአዲስ አበባ ተገንብተዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ፥ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ከኮሪደር ልማት ስራ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ሜዳዎችም ወጣቶችን ከአልባሌ ስፍራዎች በመታደግ ወደ ሜዳ እንዲመለሱ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ ብቻ የወጣቶችን የእግር ኳስ ፍላጎት የሚጨምሩ ከ1 ሺህ በላይ አነስተኛ መጫወቻ ሜዳዎች መገንባት ተችሏል ነው ያሉት።

የሚሰራው የኮሪደር ልማት በቀላሉ ሊታይ አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥አሁን አሁን በከተሞች የሰዎች መስተጋብር መጨመሩን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝም በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞች ውበትን ከመጨመር ባለፈ የሰዎች የኑሮ ዘዬ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል።

በዚህም ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ባስፋፋን ቁጥር በዘላቂነት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት መሰረት እንጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም