ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በዘመናዊ እርባታና እና በእሴት ሰንሰለት ላይ የሚገጥሙ ችግሮች መፍታት ላይ ተኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በዘመናዊ እርባታና እና በእሴት ሰንሰለት ላይ የሚገጥሙ ችግሮች መፍታት ላይ ተኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018 (ኢዜአ)፡- ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ዘመናዊ የአረባብ ስርአትን መዘርጋት እና በእሴት ሰንሰለት ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን መፍታት የርብርብ ማዕከላችን ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ ፡፡
በተቀናጀ የእንስሳት ልማት፣ የስጋ ወጪ ንግድ፣ የእርድ እንስሳት አቅርቦት ትስስር ላይ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ተጠቃሽ ቁጥር ያለው የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡
ወደ ውጭ የሚላከውም ካለን አቅም አኳያ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመስኩ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የእንስሳት እርባታውን ዘመናዊ ማድረግ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸው ዘመናዊ እንስሳት እርባታ ማዕከላትን ወደ ስራ ማስገባት በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማንሳት፥ ዝርያ ማሻሻል ላይም የተሰሩ ስራዎች ለውጥ እያመጡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ለእንስሳት ምርት ማደግ የመኖ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን አመልክተው በመኖ አቅርቦት ላይ ባለሃብቱን በስፋት ለማሳተፍ የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በእንስሳት አቅርቦት ውስጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ጨምሮ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩ አስረድተዋል፡፡
ቄራዎችንና ህብረት ስራ ማህበራትን በማገናኘት አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችል ስልት መቀየሱንም ተናግረዋል፡፡
የእንስሳት ጤናን ማስጠበቅ በዘርፉ የሚገኘው ጥቅም ከፍ እንዲል የላቀ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ በዚህም ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው የእንስሳት ዘርፍ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሚጠበቀውን ውጤት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ውይይቱ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል፡፡