ቀጥታ፡

በመንግስትና በህዝብ የተቀናጀ ትብብር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂ የልማት ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፡-በመንግስትና በህዝብ የተቀናጀ ትብብር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አስደናቂ የልማት ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ነው።

በመደበኛ ስብሰባው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምላሽና ማብራሪያቸው፤ 2017 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የታሪክ እጥፋት ውስጥ ይቻላሉ ተብሎ የማይታሰቡ ጉዳዮች የተቻሉበት የስኬት ዓመት እንደነበር ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ያነገባቸውን ዓላማዎችና ያስገኛቸውን ውጤቶች አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአንድ ዘርፍ ላይ ተንተርሶ ከድህነት ሊወጣ አይችልም በሚል ብዝኅ ዘርፍና ብዝኃ ተዋናይ የኢኮኖሚ አቅጣጫ ላይ የተነደፈው ፖሊሲ በእጅጉ ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎች ሳይዘነጉ አምስቱ ግንባር ቀደም የተሰናሰሉ በብዝኅ ዘርፍ ቢመሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚያሻሽሉ እምነት መጣሉን አስረድተዋል።  

ግብርና እና ማዕድን ለኢንዱስትሪ ግብዓት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢንዱስትሪውም ግብርናን የሚያፋጥን ማሽን ፈጣሪ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂ የታከለበት ብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማትም ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የብዝኅ ተዋናይነትም መንግስት አንድ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በመሆን ከግሉ ዘርፍ፣ ከህዝብና የልማት አጋሮች ጋር ተሳስሮ የኢትዮጵያን ልማት በየፈርጁ ማፋጠን አለበት የሚል እምነት መያዙን ገልጸዋል።

የግልና መንግስት አጋርነት እሳቤ ያለ ቢሆንም የመንግስትና ህዝብ አጋርነት ግን ግልጽ አቅጣጫ የተቀመጠለት ከለውጡ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም በመንግስት የህዝብ አጋርነት ኢትዮጵያ በርካታ ስኬቶች ማስመዝገቧን ጠቅሰው፤ ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ 48 ቢሊየን ችግኞች ስኬት ማሳያ ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ ችግኝ ከጅምሩ እስከ ተከላ መርሃ ግብሩ ባለው ሂደት አንድ ዶላር ቢወስድ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ 48 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ማድረግ መቻሏን አስረድተዋል።

በዚህም ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን ያለመታከት ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን በመስጠት በየዓመቱ ስለሰሩ ይህን ያክል ሃብት ያስወጣ የነበረን ስራ በመንግስትና በህዝብ የተቀናጀ ትብብር ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም