ቀጥታ፡

በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ትሪሊየን ብር ገቢ ይጠበቃል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፡- በ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት ገቢ አንድ ትሪሊዮን ብር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

በመደበኛ ስብሰባው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምላሽና ማብራሪያቸው÷ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ያነገባቸውን ዓላማዎችና ያስገኛቸውን ውጤቶች አብራርተዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ፖሊሲ በብዝኃ ዘርፍና ብዝኅ ተዋናይ መመራት አለበት የሚለው የፖሊሲ ትልም ተጨባጭ ሀገራዊ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዋና ዋና አቅጣጫዎች  ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ተዛብቶ የቆየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስት በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተረከበውን የተዛባ ኢኮኖሚና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ማረቅም የማሻሻያው ዋነኛ ዓላማ ነው ብለዋል።

የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻልና በማዘመን ምቹ ምህዳር መፍጠርም ሌላኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃግብር አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል።

የዘርፎችን ምርታማነትና የተወዳዳሪነት አቅም ማሳደግ፣ የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ፣ ዘላቂ ፋይናንስ ሥርዓትና ጥራት ያለው ዕድገት ማረጋገጥ ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት አካል የነበረው የገቢ ማሻሻያ ሥርዓትንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ  በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ መደረጉን አስረድተዋል። 

በዚህም በለውጡ ጊዜ የመንግስት ገቢ 170 ቢሊየን ብር እንደነበር በማንሳት አሁን ላይ አንድ ትሪሊየን ብር ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የማሻሻያ መርሃግብሩ ሳይጀመር 2016 ዓመቱን ሙሉ የነበረውን የወጪ ንግድ በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት አራት ወራት ብቻ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።

በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ የሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም