በሶማሌ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማትን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማትን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ጅግጅጋ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፡-በሶማሌ ክልል የእንስሳት ሃብት ልማትን በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ገለጸ።
በእንስሳት ሀብት ከሚታወቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል የሶማሌ ክልል አንዱ ነው።
ክልሉ አርብቶ አደሮች በስፋት የሚገኙበት በመሆኑም የእንስሳት ሀብት ልማቱን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማሳደግ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በክልሉ የአርብቶ አደር ልማት ቢሮ የእንስሳት ምርት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ አብዱላሂ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ እንስሳት ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ክልሉ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት እንዳለው ያነሱት አቶ አብዱላሂ፤ ይሁንና ያለውን ሀብት በሚመጥን መልኩ ልማቱ ተጠናክሮ ባለመሰራቱ የዘርፉን ጥቅም ማሳደግ አለመቻሉን አስታውሰዋል።
በክልሉ ያለው የእንስሳት ሀብት ከ40 ሚሊዮን በላይ እንደሚገመት ገልጸው፤ በተለይም ከለውጡ ወዲህ ይህንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እንዲያስችል የእንስሳት ጤናና ዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
ለአብነትም ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስድስት የእንስሳት ጤና ምርመራ ማዕከላት ተገንብተው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃግብርም የእንስሳት ሀብት ልማቱ ዝርያን በማሻሻል ላይ በማተኮር ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጥር መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የወተት ምርትን ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሊትር በላይ ለማድረስና የዶሮና እንቁላል ምርትም በበጀት ዓመቱ ወደ 118 ሚሊዮን ለማሳደግ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግም የእንስሳት ጤና አጠባበቅ እና የከብቶችና የዶሮ መኖ በብዛት ማምረት ላይ ትኩረት መደረጉን ተወካዩ ገልጸዋል።
የማር ምርትን ከ57 ሺህ ቶን በላይ ለማድረስ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ማሰራጨት ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።