ቀጥታ፡

በ2017 ዓ.ም የግብርናው ዘርፍ የ7 ነጥብ 3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ በ2017 ዓ.ም የግብርናው ዘርፍ የ7 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በ2017 ዓ.ም 7 ነጥብ 3 የግብርናው ዘርፍ እድገት ማስመዝገቡንና ከዓመታዊ ጥቅል እድገት (ጂዲፒ) 2 ነጥብ 3 ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።

የግብርናው ዘርፍ ከለውጡ ማግስት በኋላ ከፍተኛ ለውጥ እና እድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሩዝ ምርት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር አውስተው በ2017 ዓ.ም ምርቱ 63 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን ጠቁመዋል።

በ2010 ዓ.ም የስንዴ ምርት 47 ሚሊዮን ኩንታል ይመረት እንደነበር አንስተው፤ በ2017 ዓ.ም ባለፈው ዓመት ከ280 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት መቻሉ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

የስንዴ ምርቱ እድገት የበርካታ አድካሚ እና አታካች ስራዎች ውጤት ነው ብለዋል።

በ2010 ዓ.ም የቡና ምርት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እና የ700 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

በ2017 ዓ.ም 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና በማምረት እና የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።

ግብርናው ያመጣው እምርታ እና ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም አርሶ አደሮች እና የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም