የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአርባምንጭ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአራት ነጥብ አምስተኛ፣ አርባምንጭ ከተማ በሁለት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱ ክለቦች በ2017 ዓ.ም በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል።
ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ በሳምንቱ ከሚጠበቁ መርሃ ግብሮች መካከል ይገኝበታል።
በሊጉ ባህር ዳር ከተማ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ኢትዮጵያ ቡና በሶስት ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡድኖቹ በፕሪሚየር ሊጉ ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በነበራቸው ግንኙነት በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል።
በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ከተማ 11፣ ኢትዮጵያ ቡና ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ምድረገነት ሽሬ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምድረገነት ሽሬ በአራት ነጥብ ስድስተኛ፣ በሊጉ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። መቻል በአራት ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ቡድኖች በ2016 ዓ.ም እስከ መጨረሻው ሳምንት ዋንጫውን ለማንሳት ያደረጉት ፉክክር የሚዘነጋ አይደለም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።