ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ወሳኝ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በ16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከታንዛንያ አቻውጋር ዛሬ ያደርጋል።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይካሄዳል።

ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ታንዛንያ አይሻ ጁማ እና ጃሚላ ራጃብ ግቦች 2 ለ 0 አሸንፏል።

ሉሲዎቹ ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ ወደ ድሬዳዋ በማቅናት ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። 

የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል። 

በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ የነበረውን የማጥቃት እና ፍሰት ያለው ጨዋታ የማድረግ ድክመት አርሞ መግባት ይጠበቅበታል።

በባካሪ ሺሜ የሚመራው የታንዛንያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ከመልሱ ጨዋታ በኋላ በዳሬ ሰላም ዝግጅቱን አድርጓል። 

ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ በውድድርና የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ሲገናኙ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስድስት የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናቸው  ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ኢትዮጵያ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ስታስቆጥር ታንዛንያ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

የሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ቡድኑ በመጀመሪያው ጨዋታ የታዩ ድክመቶችን በማረም ጨዋታውን ለማሸነፍ ይገባል፤ ውጤቱን ቀልብሰን እናልፋለን የሚል እምነት አለኝ ሲል ከጨዋታው በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል። 

የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ ቡድኑ ውጤቱን ለመቀልበስ መዘጋጀቱንና በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ ገልጻ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርባለች። 

የታንዛንያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ባካሪ ሺሜ በአጠቃላይ ድምር ውጤት እናልፋለን፤ ለጨዋታው አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል ሲል ተናግሯል። 

ሉሲዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በመልሱ ጨዋታ ከሶስት እና ከዚያ በላይ ጎል በማስቆጠር ማሸነፍ ይጠበባቸዋል።

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ በሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ታረጋግጣለች።

እ.አ.አ በ2026 በሚካሄደው 16ኛው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም