ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን የቀለበሰ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ነው-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን የቀለበሰ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ነው-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውሃውን ብቻየን ልጠቀም የሚሉ ሀገራትን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ በመቀልበስ የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ቁልፍ የትብብር መሰረት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ልማት ስኬት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተማማኝ የውሃ ፍሰት በመፍጠር ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ በረከት እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አስጀምረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ያከናወነቻቸውን የልማት ስራዎች ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማስገንዘብ የውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ወደ 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለውሃ ሃብት ዘላቂ ልማት አቅም መፍጠሯን ተናግረዋል።
የተተከሉ ችግኞች በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማስቻል ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ በረከት እየሰጡ መሆኑን አንስተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ላይ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ወቅት ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያከናወነችውን የትብብር ተግባራት የማስገንዘብ ስራ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ፣ የነፋስ፣ የጸሐይና የኒውክሌር የኃይል አቅርቦት ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ በቀጣናው አስተማማኝ የሆነ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ እያደረገች ያለው ኢንቨስትመንት የጎረቤት ሀገራትን የበረከቱ ተቋዳሽ እያደረገ ነው ብለዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን በመቀልበስ የተፋሰሱን ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ወሳኝ የልማት ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ማንንም ሀገር የሚጎዳ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በጋራ እንጠቀም የሚለው መርህ የሁልጊዜም አቋማችን ነው ብለዋል።
አንዳንድ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትም ውሃው የኔ ነው፤ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለው አቋማቸው እንደከሸፈ ሊገነዘቡ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ይልቁንም ወደ ናይል የትብብር ማዕቀፍ በመግባት በአንድ ጥላ ስር መመካከር እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ከክረምት እስከ በጋ አስተማማኝ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኃይል ትስስር ጉልህ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለሚቀጥሉት አምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው 2ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ማስጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ላይ የውሃ ሃብት አጠቃቃም፣ አስተዳደርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የጋራ ተጠቃሚነት ተሞክሮዎችን የሚዳስሱ የፓናል ውይይቶችና ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅተዋል።