ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በትብብር ላይ ለተመሰረተ የውሃና ኢነርጂ ልማትና ለአፍሪካ መር መፍትሔዎች ስትራቴጂካዊ ሚና እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ የአጋርነት ሳምንትን በማዘጋጀት አፍሪካ መር የዘላቂ ልማት መፍትሔዎችን የማፍለቅ ስትራቴጂካዊ ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ የውሃ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የሴኔጋል የውሃ ሚኒስትር ቼይክ ቲዲያኔ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተገኙት የአፍሪካ የውሃ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የሴኔጋል የውሃ ሚኒስትር ቼይክ ቲዲያኔ (ዶ/ር) የስልጣኔ ምድር፣ የአፍሪካዊያን የማንነታቸው መገለጫና የመመካከሪያ መዲና በሆነችው በተደረገላቸው አቀባበል ትልቅ ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

በርካታ አፍሪካዊያን አሁንም ድረስ የንጹህ መጠጥ ውሃና የታዳሽ ኃይል አቅርቦት እያገኙ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

በአህጉሪቱ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ ወንዞች በርካታ ሀገራትን በማገናኘት ድንበር ተሻጋሪ ሃብቶች መሆናቸውን በማንሳት፥ ይህም በትብብር ዘላቂ ልማት እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚጋሩ የአህጉሪቷ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ለትብብርና ለልማት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የውኃና ኢነርጂ ሳምንትን በማዘጋጀት በውሃና ኢነርጂ ልማት ያሉ ወርቃማ ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በመለየት አፍሪካ መር መፍትሔ መገንባት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ መድረክ መፍጠሯንም አስረድተዋል።

በውሃ ሃብት ላይ በትብብር መስራት ለሰላም፣ ለልማትና ቀጣናዊ ውህደት ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።

በአህጉሪቱም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለጋራ ተጠቃሚነት በማዋል ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም የውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም የኃይል አቅርቦት ኢንቨስትመንትን ማስፋት የሚያስችል ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

የውሃ ሃብት ልማት ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቅነሳና ሌሎች የልማት አጀንዳዎች ወሳኝ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሳምንቱ ላይ የውሃ ሃብት አጠቃቀም፣ አስተዳደርና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የጋራ ተጠቃሚነት ተሞክሮዎችን የሚዳስሱ የፓናል ውይይትና ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም