ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶችን በመተግበር ያሳየችው ተሞክሮ ወደሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት ለማስፋት ይሰራል -የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስምምነቶችን በመተግበር ያሳየችውን ተሞክሮ ወደሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት ለማስፋት እንደሚሰሩ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 2ኛውን የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት በሳይንስ ሙዚየም አስጀምረዋል።

በዚህ ወቅት የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ(ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ምሳሌ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ትገኛለች።


 

የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንቱ ውሃና ንፁህ ኢነርጂን መጠቀም ለዘላቂ እድገት በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ከዘላቂ የልማት ግብና ሌሎች ከውሃ፣ ኢነርጂ፣ አካባቢና አየር ንብረት የተገናኙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተሰናሰለ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም፣ የአረንጓዴ ሽፋን እንዲጨምርና የካርበን ልቀት እንዲቀንስ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ወደተግባር ለመቀየር የምታከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

መርሃግብሩ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችልና በተፋሰሱ ሀገራት በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባውና የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ እውቅና የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ በ1999 የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው፤ በፍትሃዊ አጠቃቀምና ተጠቃሚነት ዘላቂ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማትን ማረጋገጥን ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ትብብር፣ ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ፀጥታን የማረጋገጥ ግብን ያነገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

2ኛውን የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት መሪ ሃሳብ ኢኒቬቲቩ የያዘውን ግብ ወደአገራዊ ተግባር መቀየር ጋር የተሰናሰለ ነው ብለዋል።

በናይል ተፋሰስ የውሃ ሀብት ላይ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ድንበር ዘለል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ፣ ፀሀይ፣ ንፋስና የመሳሰሉት የታዳሽ ኃይል ሀብት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ስለሆነም በአገራት ያለውን ውጤታማ ስራ ማስተዋወቅና ዘላቂ የልማት እቅድና አጋርነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ተሞክሮ በማስፋት ንፁህና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት የተፋሰሱን ሀገራትና የአህጉሪቷን ህዝብ ብልፅግና ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም