የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዞኑን የልማት አቅሞችና ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ ተጨማሪ አቅም ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዞኑን የልማት አቅሞችና ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ ተጨማሪ አቅም ነው
ዲላ፤ ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ)፡-የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዞኑን የልማት አቅሞችና ባህላዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ ተጨማሪ አቅም መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ መደበኛ ስርጭቱን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።
በወቅቱ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንደገለጹት የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ የጌዴኦን የልማት አቅሞች ባህላዊ እሴቶችና የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና አብሮነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና አለው።
የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ መደበኛ ስርጭት መጀመሩ በዚህ ረገድ የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ በተለይ የጌዴኦን ባህላዊ እሴቶችና የቱሪዝም ሃብቶች በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ድርሻቸው የጎላ ነው ብለዋል።
ጣቢያው የህዝቦችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ ሀገራዊና አካባቢያዊ ልማቶችን ለማፋጠንና የመረጃ ፍሰትን ለማሳለጥ ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የማህበረሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የጌዴኦ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በሙከራ ደረጃ ቆይቶ ዛሬ መደበኛ ስርጭት መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የጣቢያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ በቀለ ናቸው።
የህዝብን ባህልና ቋንቋ፣ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲሁም የልማት ውጥኖችን በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ጣቢያው ጌዴኡፋንን ጨምሮ በሦስት ቋንቋዎችና በተለያዩ ይዘቶች የ24:00 ሰዓት ስርጭት እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
የጌዴኦ ቴሌቪዥን ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ፀጋዬ ኦብሴ በበኩላቸው ጣቢያው የህዝቦችን ትስስር በማጠናከርና ገዥ ትርክትን በመገንባት ረገድ ትልቅ ሥራ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተለይ የሰላም እሴቶችን በማጉላትና በህብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ ለህዝቦች አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለቴሌቪዥን ጣቢያው መቋቋም አስተዋጾ ላበረከቱ አካላት እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል።