በሲዳማ ክልል የመንገድ መሰረተ ልማት ጥራትን ማረጋገጥና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የመንገድ መሰረተ ልማት ጥራትን ማረጋገጥና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል
ሀዋሳ ፤ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል የመንገድ መሰረተ ልማት ጥራትን ማረጋገጥና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የሶስት ወራት እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ በሀዋሳ መክሯል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የመንገድ ልማት ጥራትን ለማረጋገጥና የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል።
ባለፉት ሶስት ወራትም የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግ የዲዛይን፣ የማሽነሪ ጥገና የግብዓት አቅርቦትና አማካሪ ድርጅቶችን የመለየት የዝግጅት ምእራፍ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 132 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ስራ መከናወኑንና ለህብረተሰብ ተሳትፎ ለሚገነቡ መንገዶች የንቅናቄ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥራትን ለማረጋገጥ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን የአንድ ማእከል አገልግሎት መጀመሩና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በቅንጅት መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም "ሲዳማ ዲጂታል ትራንስፖርት" የተሰኘ አዲስ ሶፍትዌር በማበልጸግ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር መሰረተ ልማት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ዘገዬ አሜሶ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለመንገድ መሰረተ ልማት ከፍተኛ በጀት መድቦ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ የተከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ማቀላጠፋቸውን ጠቁመዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሲዳማ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምክትል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ፍቅሬ ዮሳ ናቸው፡፡
ትርፍ ማስከፈልና መጫን እንዲሁም የትራንስፖርት ህጉን በጣሱ ከ13 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
በዘርፉ ላይ የሚደረግ የማዘመን ስራ የትራፊክ አደጋን የመከላከል ስራን ከማገዝ አንጻርም ጉልህ ሚና ያለው መሆኑንና እንዲሁም የተጀመረው ትኩረትና ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ያለፉት ዘጠና ቀናት እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ምክክር የተደረገ ሲሆን በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡