በክልሉ የተማሪዎች ውጤት መሻሻልን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተማሪዎች ውጤት መሻሻልን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የታየውን የተማሪዎች ውጤት መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል የትምህርት ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
"ብቁ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ አጠቃላይ የትምህርት ሴክተር ዓመታዊ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በተሰራው ሥራ በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል እየታየ መጥቷል።
የትምህርት ሥብራትን ለመጠገን ባለፉት ዓመታት ባለድርሻ አካላትን ባማሳተፍ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ከማድረግ ጀምሮ የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የገለጹት።
ለአብነትም በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መጀመሪያ በክልሉ በ12ኛ ክፍል ሰባት በመቶ ብቻ የነበረው ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ምጣኔ በአሁኑ ወቅት 15 በመቶ መድረሱን ጠቅሰዋል።
እየተሻሻለ የመጣውን የተማሪዎች ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለተማሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።
በክልሉ ትምህርት ቤቶችን የፈጠራ ማዕከል ለማድረግና ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸውን ትውውቅ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
የሳይንስና የፈጠራ ሥራዎች በትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ደስታ አስታውቀዋል።
በጉባኤው በ2017 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እንደውጤታቸው የገንዘብ፣ የላፕቶፕ እና የዴስክ ቶፕ ሽልማት ተበርክቷል።
በጉባኤው የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።