ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በማስተሳሰር ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላም፣ልማትና ብልጽግና ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በማስተሳሰር ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላም፣ልማትና ብልጽግና ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ሀይል በማስተሳሰር ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላም፣ልማትና ብልጽግና ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 2ኛውን የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት በሳይንስ ሙዚየም አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ውሃና ኢነርጂ የኢንዱስትሪዎችን የሀይል አቅም በማሳደግ ነገን የሚያበስሩ የሽግግር ሞተሮች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል፣ለውሃ እና ለአረንጓዴ ልማት በሰጠችው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቷን በመግለጽ፤የንጹህ ውሃና የታዳሽ ሀይል ስርጭትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የንጹህ ሀይል ተጠቃሚ መሆናቸውን በማንሳት፤እንደ ሀገር የተፈጠረው የሀይል አቅም ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለጂቡቲ፣ለሱዳንና ለኬንያ ታዳሽ ኃይል እያቀረበች ነው፤ በቅርቡም ለሌሎች ሀገራት መላክ ትጀምራለች ብለዋል።
የአፍሪካ መፃኢ ዘመን ተስፋ፣የቁርጠኝነትና የአንድነታችን ምልክት የሆነው የሕዳሴ ግድብ የራዕያችን ማዕከል ነው ብለዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ የንጹህ ሀይል ምንጭ በመሆን በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ከኃይል ልማት ባሻገር ለብዝኃ ህይወት ጥበቃ፣ጎርፍን ለመከላከል እና በታችኛው ተፋሰስ ላሉ ሀገራት የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ እና ሌሎች ወንዞቿ ከድንበር አጥር በላይ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በፍትሐዊነትና በጋራ ለመበልጸግ የአንድነት ድልድዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ2019 ጀምሮ 48 ቢሊዮን ችግኞችን መትከሏን አስታውሰው፤አንድ ሶስተኛውን በናይል ተፋሰስ በመትከል ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ያላትን አበርክቶ አሳይታለች ብለዋል፡፡
"እያንዳንዱ የውሃ ጠብታ፣ እያንዳንዱ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል ህዝባችንንና ምድርን በአግባቡ ሊያገለግል ይገባል" ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለነገ እጣ ፋንታችን የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የባህር በር ማግኘት ንግድን ለማጠናከር፣የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጎልበትና ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ከጎረቤቶቿ ጋር የተሳሰረ መሆኑን በመጥቀስ፤በጋራ ለመልማት እና ዘላቂ ጥቅምን ለማስጠበቅ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እየሠራች ነው ብለዋል።