ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ነው - የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ነው - የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አፍሪካዊያንን አንድ በሚያደርጉ አሰባሳቢ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ነው ሲሉ የቀድሞ የማላዊ ፕሬዝዳንትና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የማላዊ ፕሬዝዳንት ጆይሴ ባንዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን በሚያሰባሰቡ የጋራ ዓላማዎች ዙሪያ ተጠቃሽ ሚና እየተጫወተች ነው።
በቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአሁኑ አፍሪካ ኀብረት ምስረታ ሂደት የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ መሆኑንም አስታውሰዋል።
በአፍሪካ ሠላምና አንድነትን ማረጋገጥ የተሻለች አህጉርን የመገንባት ግብን ለማሳካት ወሳኝ እንደሆነ በማንሳት፥ አፍሪካውያን በጋራ ተቀራርበው እየተወያዩ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጡባቸው መድረኮች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የጣና ፎረምን በመመስረት ችግሮቻችንን እንድንፈታ እያሰባሰበችን ነው ያሉት ጆይሴ (ዶ/ር)፥ አፍሪካን አንድ በሚያደርጉ አጀንዳዎች ላይ እየተጫወተች ያለው ሚና የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በልማት በኩልም የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎችን በማስተባበር እያስመዘገበ ያለው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ተንታኝ ፓ ኪዌሲ ሄቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አፍሪካውያን በአንድ ተሰባስበው የፖለሲ መፍትሄዎችን እንዲቀይሱ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ድልድይ ሆና እያገለገች ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የኢትዮጵያን ፈለግ በመከተል ለአፍሪካ አንድነት መጠናከር ሊረባረቡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአፍሪካ ልንፈታቸው የለየናቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ እንደ ድልድይ ሆነው የሚያስተባብሩ በርካታ ተዋንያን ይፈልጋሉ ያሉት ፕሮፌሰሩ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ምሳሌ መሆን የምትችል ሀገር ናት ብለዋል።