ቀጥታ፡

አስተዳደሩ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ከመመከት አንጻር እያሳየ ያለውን ውጤታማ ሥራዎች ማጠናከር ይገባዋል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሀገር ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ከመመከት አንጻር እያሳየ ያለውን ውጤታማ ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ሀገራዊ የሳይበር ቁጥጥርን ከማጎልበት አኳያ ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ተልዕኮ ተኮር ምርትና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያም ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቁልፍ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባቱን ጠቁመው፤ በሩብ ዓመቱ ለተመዘገቡ 13 ሺህ 443 የጥቃት ሙከራዎች ምላሽ መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ በርካታ አገልግሎቶች ተደራሽ መደረግ መቻላቸውን ጠቁመው፤ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ አስተዳደር ስርዓት ተጠናቆ በይፋ መመረቁንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሩብ ዓመቱ የኤሮ-አባይ የድሮን ማምረቻ፣ የኮንስትራክሽን ሬጉላቶሪ ስርዓት፣ ለበርካታ ከተሞች የካደስተር ኢ-ላንድ መተግበሪያን ጨምሮ ሌሎችንም ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትም የተቋሙን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም በማድነቅ ምላሽና ማብራሪያ የሚፈልጉ ጉዳዮችንም አቅርበዋል።

ከእነኚህም መካከል የሀገርን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና የሳይበር ጥቃትን ቀድሞ ከመከላከል አንጻር የተቋሙ አሁናዊ ቁመና ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የተቋሙ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጋርነት፣ ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከውጤት አንጻር ምን ማሳያ አለው የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ የሳይበር ደህንነትን ከማስጠበቅ አኳያ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ የምላሽ አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤የተቋሙ ዝግጁነትም እያደገ መሆኑን አንስተዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ፍቅረስላሴ ጌታቸው ተቋሙ የተለያዩ ስምምነቶችን ከመፈራረም ባሻገር ስምምነቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ ትልቅ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢንፎርሜሽን አሹራንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ሃኒባል ለማ በበኩላቸው፤ የስትራቴጂክ ዕቅዶችን በሶስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፤ ይህም የመሰረተ ልማት ግንባታንና ሥራን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሰቢ ፈቲህ ማሕዲ (ዶ/ር) በሰጡት ማጠቃለያ፣ አስተዳደሩ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ከመመከት አንጻር እያሳየ ያለውን ውጤታማ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በቅድመ መከላከልና ዝግጁነት የተሰሩ አበረታች ሥራዎችን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመው፤ ተቋሙ ብቁ የሰው ኃይልን ከማፍራት አኳያ የጀመራቸውን ውጤታማ ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም