ቀጥታ፡

ተኪ ምርት አምራቾች የመንግሥት የግዥ መመሪያ የሰጣቸውን ሰፊ የገበያ ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ተኪ ምርት አምራቾች የመንግሥት የግዥ መመሪያ የሰጣቸውን ሰፊ የገበያ ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ጥሪ አቀረቡ።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ለአምራች ዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በተመለከተ ለዘርፉ ተዋንያን ማብራሪያ ሰጥቷል።


 

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የግዥ መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ነው ተብሏል።

በግዥ መመሪያው በሀገር ውስጥ ለሚመረትና 20 በመቶ እሴት ለሚጨመርባቸው እንዲሁም በመልሶ መጠቀም ለሚመረቱ ምርቶች ቅድሚያ የሚሰጥበት ዕድል ተመቻችቷል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አምራቶች ከውጭ ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ምርቶች ተኪ ምርት አምራቾች ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራት ያለው አመኔታ ዝቅተኛ መሆንና የአመለካከት ክፍተት የገበያ እድሎችን እንዳንጠቀም የራሱ አሉታዊ ውጤት እንዳለው በምክንያትነት አንስተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል መንግሥት የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሕግና አሰራር ማሻሻያዎችን ከማድረግ ባለፈ የገበያ ትስስርን ለማሳደግ ተጨባጭ ሥራዎች እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ፣ አሁን ያለው የመንግሥት ግዥ መመሪያ የሀገር ውስጥ አምራችነትን የሚያበረታታና ገቢ ምርትን ለመተካት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ሀገር ውስጥ ከሚመረቱ ምርቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ለማስቀረት ተጨማሪ ቀረጥ ይጣላል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾች በመንግሥት ተቋማት የተፈጠረውን የግብይት ሥርዓት በመጠቀም የገበያ ዕድላቸውን እንዲያሰፉ አስገንዝበዋል።

መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ግዥን በስፋት እየተጠቀመ ቢሆንም የግዥ መመሪያውንና አሠራሩን በአግባቡ አለመጠቀም እንደሚስተዋል አመልክተዋል።

በመሆኑም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለውጭ ገበያ ምርቶችን የማቅረብ ዕድላቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፣ ተኪ ምርት አምራቾች በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪነታቸው እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

እሴት ለጨመሩ ኢንዱስትሪዎች የሚደረገው የ20 በመቶ ማበረታቻ አምራችነትን የሚያበረታታ መሆኑን ነው የተናገሩት።


 

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ፥ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓቱ ቀልጣፋ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመንግሥት ተቋማት ጥራት ያላቸው ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል።

የመንግሥት የግዥ መመሪያው ግልጽ የጨረታ ሂደትን ከመከተል ጀምሮ አምራች ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቃ መሆኑን ጠቅሰው፥አምራቹ ስለ ግዥ አዋጁና መመሪያው ያለውን ግንዛቤ የበለጠ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም