ቀጥታ፡

የክልሉ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ)፦የአማራ ክልል ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የማዕረግ ዕድገት፣ዕውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የክልሉ ፖሊስ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቅ በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የፖሊስ ሃይሉ ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ፅንፈኛ ኃይሉ ክልሉን ለማተራመስ ያቀደውን ሴራ በመቀልበስ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የላቀ ሚናውን ተወጥቷል ብለዋል።


 

በመሆኑም የፖሊስ አባላትና አመራሮች እየተወጡት ላለው ግዳጅና ተልእኮ አድናቆታቸውን በመግለጽ የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በዛሬው እለት የተሰጠው እውቅና እና ሽልማትም በቀጣይ ለላቀ አፈፃፀም እንዲዘጋጁ እና ሌሎች ጀግኖችንም ለማፍራት የሚያነሳሳ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉን ሰላም የማፅናት ስራ ውጤታማነት ከፍ ለማድረግም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለማስፋት የተጀመረው የሪፎርም ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የህዝቡ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠበቅና ልማቱ እንዲፋጠን የተጀመረው የህግ ማስከበር ተግባርም በላቀ ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የክልሉ ፖሊስ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ልማቱን ለማፋጠን የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ቡድን በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በመቀልበስ አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ውጤታማ ተግባራት ማከናወን መቻሉን አመልክተዋል።

በየደረጃው ዛሬ የተሰጠው የማዕረግ ዕድገት፣ዕውቅናና ሽልማትም ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፥ይህም ሰራዊቱን ለበለጠ የግዳጅ አፈፃፀም እንዲዘጋጅ ያደርጋል።

የረዳት ኮሚሽነር ማዕረግ ዕድገት ያገኙት አየሁ ታደሰ በበኩላቸው፤ የተሰጣቸው ዕውቅናና የማዕረግ እድገት ለላቀ ግዳጅ አፈፃፀም አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ሶስት የምክትል ኮሚሽነር ማዕረግና ስምንት የረዳት ኮሚሽነር ማእረግን ጨምሮ ለሌሎች የፖሊስ አመራሮችና አባላት የማዕረግ ዕድገት፣ዕውቅናና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎችና የፖሊስ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም