አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና አትሌት ትዕግስት አሰፋ የዓለም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች እጩዎች ውስጥ ተካተቱ - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና አትሌት ትዕግስት አሰፋ የዓለም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች እጩዎች ውስጥ ተካተቱ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ)፦ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና አትሌት ትዕግስት አሰፋ የዓለም የዓመቱ ምርጥ አትሌቶች ከስታዲየም ውጪ ዘርፍ እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የዓለም ምርጥ አትሌት የተለያዩ ዘርፍ እጩዎችን ይፋ እያደረገ ይገኛል።
የአትሌቲክሱ የበላይ አካል ዛሬ ባወጣው መረጃ ከስታዲየም ውጪ የዓለም ምርጥ አትሌት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ በወንዶች አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሴቶች አትሌት ትዕግስት አሰፋ መካተታቸውን አስታውቋል።
ታንዛንያዊው አልፎንስ ሲምቡ፣ ኬንያዊው ሰባስቲያን ሳዌ፣ ብራዚላዊው ካዮ ቦንፊም እና ካናዳዊው ኢቫን ደንፊ ሌሎች የወንዶች እጩዎች ናቸው።
በትውልድ ኢትዮጵያዊቷ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው ሲፋን ሀሰን፣ ኬንያውያኑ ፔሬዝ ጄፕቺርቺርና አግነስ ንጌቲች እንዲሁም ስፔናዊቷ ማሪያ ፔሬዝ በሴቶች ዘርፍ ተካተዋል።
ከስታዲየም ውጪ የዓለም ምርጥ አትሌት ድምጽ አሰጣጥ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
በድምጽ አሰጣጡ ሂደት የዓለም አትሌቲክስ የባለሙያዎች ምክር ቤት 75 በመቶ እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ አባላት እና የሕዝብ ድምጽ 25 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ገልጿል።
ምክር ቤቱና የአትሌቲክስ ቤተሰብ አባላት ድምጻቸውን በኢ-ሜይል የሚሰጡ ሲሆን ሌሎች የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች በዓለም አትሌቲክስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ አማራጮች መስጠት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የ2025 የዓለም ምርጥ አትሌቶች ሽልማት ህዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም በሞናኮ ይካሄዳል።