በአማራ ክልል በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የመስህብ ሀብቶችን ጎብኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የመስህብ ሀብቶችን ጎብኝተዋል
ደሴ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የመስህብ ሀብቶችን መጎብኘታቸው ተገለጸ።
የቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የቢሮ ኃላፊው መልካሙ ፀጋዬ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመስህብ መዳረሻ ሥፍራዎችን በማልማት፣ ቅርስና ሙዚየሞችን በማደስና በመጠገን አበረታች ሥራ ማከናወን ተችሏል።
በተጨማሪም በክልሉ ያሉ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ለማስተዋወቅና የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ መስህቦችን ከጎበኙ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን አስታውቀዋል።
ግሸን፣ መውሊድ፣ ሶለል፣ አሸንድዬ፣ ሻዳይ፣ እንግጫ ነቀላ፣ መስቀልና ሌሎች በዓላት በስኬት መከበራቸው ለገቢው መገኘት ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።
የበዓላቱ መከበር የክልሉን ባሕልና እሴት በመጠበቅና በማጎልበት ለትውልድ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ለቅርስና ሙዚየም እድሳትና ጥገና ከ461 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ወደ ተግባር ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቁንም የቢሮ ኃላፊው አንስተዋል።
የጣና ሐይቅ፣ ደሴት፣ ገዳማት፣ ጥንታዊ የሾንኬ መንደርን፣ አገው ፈረሰኞችን ጨምሮ በክልሉ ያሉ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችንና ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አስያ ኢሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ወራት ከግሸን ደብረ ከርቤ፣ ከመውሊድና ሌሎች በዓላት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
የሻዳይ፣ መስቀል፣ ቡሄና ሌሎችም የአደባባይ በዓላትን በስኬት ማክበር በመቻሉ የቱሪዝም ዘርፉ ተነቋቅቷል ያሉት ደግሞ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ እዮብ ዘውዴ ናቸው።
በቀጣይም የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት፣ ሙዚየምና ቅርሶችን በመጠገን፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ የተሻለ ገቢ እንዲገኝ ይሰራል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ወደ አማራ ክልል ከሚመጡ ቱሪስቶች ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የመድረኩ ተሳታፊ አመራሮችና ባለሙያዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባም ተመላክቷል።