ባህላዊ እሴቶችን በማጥናት ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወነ ነው-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ እሴቶችን በማጥናት ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወነ ነው-ሚኒስቴሩ
ሳጃ ፤ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ) ፡-ባህላዊ እሴቶችን በተገቢው በማጥናትና በመሰነድ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ተግባርን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እያከናወነ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የየም ዓመታዊ የመድኃኒት ለቀማ ስነ-ስርዓት ''ሳሞ ኤታ'' በዞኑ ቦር ተራራ ላይ ዛሬ ተካሄዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ እንዳሉት ባህላዊ እሴቶችን በማጥናት ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተከናወነ ነው።
የየም ማህበረሰብ ባህላዊ የመድኃኒት ለቀማ ስርዓትም ጤናን ከመጠበቅ ባለፈ ተፈጥሮን የመጠበቅ እሴት አካል መሆኑን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ ሀገር በቀል እውቀቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ሁለንተናዊ ጠቀሜታቸውን ለማጉላት እየሰራ መሆኑን አንስተው ለመድሃኒት የሚውሉትን እፅዋት ተንከባክቦ ማቆየት የሁሉም አካላት ኃላፊነት መሆኑንም አመልክተዋል።
የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) የየም ሃገር በቀል መድኃኒት አሰባሰብ ከፈውስ ባለፈ የአብሮነት ውጤት ነው ብለዋል። ።
ይህን እሴት ለማስቀጠል ትውልዱ የባህል መድኃኒት አዋቂዎችን ጥበብ መውረስ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በመድኃኒት ለቀማው ቦታ ላይ የተገኙት የሐረማያ ዩኒቨርስቲ የባህላዊ ህክምና መምህር እና ተመራማሪ ኤሊያስ አህመድ (ዶ/ር) እንዳሉት የየም ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በትውልድ ቅብብሎሽ የማቆየት ቱባ ባህልን ማስፋት ይገባል ብለዋል።
ይህን ተግባር በሳይንሳዊ መንገድ ለማስፋትም ዩኒቨርሲቲው ጥልቅ ምርምር በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የየም ባህላዊ መድኃኒት ለቀማና ስርዓት ከፈውስ ህክምና ባለፈ ለቱሪዝም ሀብት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ ናቸው።
በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን ተለቅሞ የሚቀመመው መድኃኒት እስከ መጪው ዓመት ድረስ እንደሚያገለግልም ገልፀዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በተራራው ላይ ካሉ በርካታ የእፅዋት አይነቶች ቅጠል፣ ስራስርና ቅርፊት በመሰብሰብ ቤታቸው ወስደው በአግባቡ በማዘጋጀት ለሰውና ለእንስሳት የሚሆኑ መድኃኒቶችን ይቀምማሉ ብለዋል፡፡
በአካባቢው የሀገር ባህል መድኃኒት አዋቂው አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም በበኩላቸው የሚቀመሙት መድኃኒቶች ህመምን ከመፈወስ ባለፈ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል ጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።
በለቀማ ስነ-ስርዓቱ ላይም አባቶች እና እናቶች ስለ መድኃኒት አሰባሰቡ ለታዳጊዎችና ወጣቶች የሚያስተምሩበት እሴት እንዳለም አስረድተዋል።
የፌደራልና የክልል አመራር አባላት፣ ከዩኒቨርስቲ የመጡ ተመራማሪዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ስነ-ስርዓቱን ታድመዋል።