ቀጥታ፡

የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ ነው - ሌተናል ሃለፎም መለሰ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የቀድሞ የባሕር ኃይል ማህበር ሊቀ መንበር ሌተናል ሃለፎም መለሰ ገለጹ።

ሌተናል ሃለፎም መለሰ ከኢዜአ ጋር በባህር በር ጉዳይ ላይ ቆይታ አድርገዋል።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያን የጠረፍ ጠባቂ በሚል በ1946 ዓ.ም በአዋጅ መሰረት የተጣለው የባሕር ኃይል እስከ ደርግ መንግስት ሥርዓት መውደቅ ድረስ በተደራጀ መልኩ መስራቱን ነው የገለጹት።

የቀድሞ ባህር ሃይል የኢትዮጵያን የባሕርና ጠረፍ አካባቢ ደኅንነት በአስተማማኝነት መልኩ መጠበቁን ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የዓባይ ወንዝና ከባህር ተጠቃሚነት ለማራቅ ከጥንት ጀምሮ ያላቆመ ሴራ መኖሩን ያስታወሱት ሊቀ መንበሩ፤ ከደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ አገሪቷ የባህር በር እንድታጣ መደረጉን ተናግረዋል።

ዓባይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ብስራትን ያሰማ መፍትሔ ማግኘቱን ጠቅሰው፥ኢትዮጵያን የባሕር በር እንዳይኖራት ለማድረግ የተሸረበው ሴራም በውጭ ባዕዳንና በውስጥ ባንዳዎች የተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ለመመለስ አጀንዳ ማድረጉን አድንቀው፥የባሕር በር የሀገር ህልውና ማስጠበቂያና የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫ መሳሪያ ነው ብለዋል።

መንግስት የባሕር በር ጉዳይ በወሳኝ አጀንዳነት ወደፊት ማምጣቱ ታላቅ ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፤የባሕር በር አልባነትም የመኖር አለመኖር የህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ተገቢ ምላሽ ለማስገኘት ዜጎች በሁሉም ዘርፍ አንድነታቸውን በማጽናት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተደረገውን ትብብር ለባሕር በር ባለቤትነት በአንድነት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም