ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ውጤታማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 17/ 2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ውጤታማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያጎለብቱ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።

4ኛው ክልላዊ የጤና ላቦራቶሪ (ቤተ-ሙከራ) ፌስቲቫል ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በፌስቲቫሉ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ እንዳመለከቱት፤ የሕብረተሰቡን ድንገተኛ የጤና አደጋ ሥጋቶች ፈጥኖ ለመለየትና ምላሽ ለመስጠት የላቦራቶሪ (ቤተ-ሙከራ) አቅምን ማጎልበት ያስፈልጋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በጤና ተቋማት የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ረገድ አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በሁሉም ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የላቦራቶሪ (ቤተ-ሙከራ) መሳሪያዎችንና ግብአቶችን ተደራሽ በማድረግ የበሽታ ምርመራ ውጤታማነትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱም በጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ጥራትና ውጤታማነት ለማሳደግ እንዲቻልም 470 ተጨማሪ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች እየተሰራጩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም በሽታን መርምሮ ፈጥኖ ፈውስ ከመስጠት ባሻገር ለምርምር፣ ለፈጠራ ሥራና ለቴክኖሎጅ ሽግግር ትኩረት በመስጠት የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ አቅም ግንባታ ዳይሬክተር ዳንኤል መለሰ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ የህክምናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ የኤች አይቪ ኤድስ፣ የቲቢ እና ወባ በሽታዎችን ፈጥኖ በመለየት ለማከምና ለመከላከል የሚያስችል አዳዲስ የላቦራቶሪ መሳሪያዎችን ተደራሽ የማድረጉ ተግባር መቀጠሉን ተናግረዋል።

የአማራ ክልልም የላቦራቶሪ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ በሀገር ደረጃ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ለሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የላቦራቶሪ ተደራሽነት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ናቸው።

እንደክልል የላቦራቶሪ ተደራሽነትን በማሳደግ ለመጣው ለውጥ የክልሉ መንግስትና የባለድርሻ አካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ የፌደራልና የክልሉ የዘርፉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም