ቀጥታ፡

በእውቀትና በሥነ ምግባር የታነጸ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን የማፍራቱ ተግባር ይጠናከራል

ደብረብርሃን ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፡- በእውቀት፣ በክህሎትና ሥነ ምግባር የታነጸ ብቁና ተወዳዳሪ  ዜጋ የማፍራትን ተግባር ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። 

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተመደቡለትን ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ዛሬ መቀበል ጀምሯል። 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ተግባር ተኮር የመማር ማስተማር ሂደትን በመከተል ተማሪዎችን በእውቀትና በክህሎት መገንባቱን ይቀጥላል። 

ተቋሙ በምርምር ላይ በመመስረት በእውቀት፣ በክህሎትና ሥነ ምግባር የታነጸ ብቁና ተወዳዳሪ  ዜጋን  በማፍራት ለሀገራዊ እድገት መፋጠን ድጋፉን እንደሚያጠናክርም እንዲሁ።

አዲስ ገቢ ተማሪዎችን "በቃል ኪዳን ቤተሰብ" ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በማስተሳሰር ቆይታቸው ይበልጥ የተመቻቸ እንዲሆን እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዲን አቶ ጊዜው ፈጠነ፤  በዋናው ግቢና  እና በመሃል ሜዳ ካምፓስ ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን ተናግረዋል።

የመማር ማስተማር ሥራውን የተሻለ ለማድረግም የተማሪዎች መኖሪያና መማሪያ ክፍሎች፣ የምግብ  ቤት፣ ቤተ መጻህፍት  የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  አገልግሎት መስጫና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች መመቻቸታቸውንም አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ኪሮስ አሸብር በበኩሉ፤ ለተማሪዎች እየተደረገ ያለው  አቀባበል ከቀድሞ  በእጅጉ የተሻለ ነው ብሏል።

የተማሪ ኮሚቴዎች ተመድበው  ከአውቶቡስ መናኸሪያና ከከተማው መግቢያና መውጫ በሮች ተማሪዎችን በመቀበል  ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን  ገልጿል።

ልጃቸውን ዩኒቨርሲቲው ድረስ ካመጡት ወላጆች መካከል ወይዘሮ ዘርፌ ቶላ በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢው ሕብረተሰብ የተደረገላቸው አቀባበል ልጃቸው በቤቱ እንደሚማር ያህል እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

"የቃል ኪዳን ቤተሰብ " መመስረቱ ደግሞ የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ወሳኝ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ  ሌላው ወላጅ መሪጌታ ኢሳያስ ደምሴ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም