አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ተጨማሪ ዕድል ይዘው መጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ተጨማሪ ዕድል ይዘው መጥተዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተገለጡ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ለዘርፉ እድገት ተጨማሪ ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው አስጎብኝ ድርጅቶች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በዘርፈ ብዙ የልማት ዘርፎች በመታገዝ የሚታይ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ በሀገሪቱ ተለይተው የተቀመጡ አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡
መንግስት ይህንኑ መሰረት በማድረግ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስፋፋት ላይ የሚገኝ ሲሆን ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለአገርና ገበታ ለትውልድ በሚሉ መርኃ ግብሮች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አዳዲስ መዳረሻዎች በመገንባት ላይ ነው፡
በዚህም በአዲስ አበባ የአንድነት፣ ወዳጅነትና እንጦጦ ፓርክ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ጨበራ ጩርጩራና ኮይሻን የመሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን የሆነውን የንጋት ሀይቅ እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተደብቀው የቆዩ ሀብቶች እንዲለሙ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስጎብኝ ድርጅቶች እንዳሉት በዘርፉ የሚከናወነው ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለቱሪዝም ማደግና ለባለድርሻ አካላት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ልማቱ አስጎብኚ ድርጅቶችን ከማነቃቃት ባለፈ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኝ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ስለሺ መሰረተ ልማቶቹ ጎብኚዎች በፈለጉት አማራጭ የፈለጉትን ስፍራ እንዲጎበኙና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተገለጡት አዳዲስ የመዳረሻ ስፍራዎች በሀገሪቱ የሚገኙትን የቱሪዝም መስህቦች በስፋት ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ እንቁ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤የቱሪዝም መሰረተ ልማት መስፋፋት የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ ባሻገር ለዘርፉ ሙያተኞች ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
የኤደን ላንድ ቱር ኤንድ ትራቭል ባለቤት አቶ እንዳልካቸው የምሩ ፤ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ትኩረት አማራጭ የመዳረሻ ስፍራዎች እንዲስፋፉ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡