ኢትዮጵያ ለቀጣናው ዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ልማት እንዲሁም ለጋራ ብልፅግና መሪ ሚና እየተወጣች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ልማት እንዲሁም ለጋራ ብልፅግና መሪ ሚና እየተወጣች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ልማት እንዲሁም ለጋራ ብልፅግና መሪ ሚና እየተወጣች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 2ኛውን የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሳምንት በሳይንስ ሙዚየም አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል፣ ለውሃ እና ለአረንጓዴ ልማት በሰጠችው ትኩረት ለውጥ እያመጣች ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የቀጣናው የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለጂቡቲ፣ ለሱዳንና ለኬንያ ታዳሽ ኃይል እያቀረበች ነው ብለዋል።
በቅርቡም ወደ ሌሎች ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምትልክ ጠቅሰው፥ ይህም የጋራ ቀጣናዊ የብልጽግና ራዕይዋ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ የላቀ ራዕይ ምሰሶ እንደሆነ ገልጸው፥ ግድቡ ጽናታችንን፣ አንድነታችንንና በአፍሪካ መጻኢ የጋራ ህልሞች ላይ ያለንን አቋም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የግድቡ አገልግሎት ከኃይል ልማት ባሻገር ለብዝኃ ህይወት ጥበቃ፣ ጎርፍን ለመከላከልና በታችኛው ተፋሰስ ላሉ ሀገራት የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።
ከፉክክር ይልቅ የጋራ ተጠቃሚነትንና ትብብርን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በማንሳትም፥ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ የቀጣናው የትስስር መሠረቶች ናቸው በሚል ግልፅ አቋም እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም በአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ባለፉት ዓመታት ከተተከሉ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች አንድ ሦስተኛ ያህሉ በዓባይ ተፋሰስ መተከላቸውንና ይህም ለሌሎች ሀገራት ፋይዳው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ኢኮኖሚያችን እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባህር በር ማግኘት ለቀጣይ እጣፈንታችን ዋስትና የሚሰጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የባህር በር ለኢትዮጵያ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር በር ማግኘት ንግድን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጎልበትና ቀጣናዊ ትብብርን ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር እጣፈንታዋ የተሳሰረ በመሆኑ በጋራ ለመልማት እና ዘላቂ ጥቅምን ለማስጠበቅ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እየሠራች ነው ብለዋል።
አፍሪካ ዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ ኢትዮጵያ መሪ ሚናዋን መወጣቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።