ቀጥታ፡

የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር አካታች እና አሳታፊ የፌዴራል ስርዓትን ለማጠናከር  እያገዘ ነው 

አዳማ ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን መከበር አካታች እና አሳታፊ የፌዴራል ስርዓትን ለማጠናከር እያገዘ መሆኑን የፌዴራሊዝምና ሕገ መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝምና ሕገ መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውንና ማንነታቸውን በተሻለ መልኩ እየገለጹ እና እያስተዋወቁ ነው።

ከእነዚህ ማስተዋወቂያ መድረኮች መካከል  የብሔሮች፣  ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤  ቀኑ መከበሩ ሕብረብሔራዊ  አንድነትና ትስስርን ይበልጥ  እያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀኑ መከበር በተለይም ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህላቸውንና ማንነታቸውን በአደባባይ እንዲያስተዋውቁ በማድረግ አካታች እና አሳታፊ የፌዴራል ስርዓትን ለማጠናከርም እያገዘ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በፌዴራሊዝምና ህገ መንግሥት አስተምህሮ ዙሪያ ግንዛቤን በማሳደግ አንድነትን ለማፅናት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከለውጡ ወዲህ የፌዴራል ስርዓቱን አካታችና ሚዛኑን ለማስጠበቅ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ከለውጡ በፊት አጋር ተብለው ይጠሩ የነበሩ  ክልሎች ከለውጡ ወዲህ እንደ ሌሎች ክልሎች ወደ ውሳኔ ሰጪነት መምጣታቸውን አውስተው፤  ይህም  ለፌደራል ስርዓቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  ትግሉ መለሰ በበኩላቸው፤  የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች   ቀን በዓል ህዝቡ በፌዴራሊዝምና ህገ መንግሥት ዙሪያ ግንዛቤው እንዲያድግ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዘንድሮም በዓሉ ሲከበር በፌዴራሊዝና በህገ መንግሥት ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ  በመፍጠር ሕዝቡ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲንሆን ይሰራል ብለዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ፌዴራሊዝም መምህር ሉል ዴቪድ፤  ከለውጡ ወዲህ የፌዴራል ስርዓቱ ሚዛናዊና አካታች እየሆነ ለመምጣቱ በርካታ አመላካች ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰዋል።


 

ከእነዚህ መካከል ታዳጊ ክልል ተብሎ ሲጠራ የቆየው የጋምቤላ ክልል  ከሌሎች ክልሎች እኩል የልማት ተሳትፎው እያደገ መምጣቱን በማሳያነት አውስተዋል።

ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ቀን በዓልም ሕብረብሔራዊ  አንድነት፣ ትስስርና ግንኙነት እንዲጎለብት እንዲሁም ሕዝቦች ማንነትና ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ትልቅ መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተዘጋጀ መድረክ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም