የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እንዲሆን እያገዘ ነው - ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እንዲሆን እያገዘ ነው - ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 17/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማሕበረሰቡን ችግሮችን በራስ አቅም በመፍታት የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እንዲሆን እያገዘ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
''በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 ዓ.ም ሀገራዊ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያና የእውቅና መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅታዊ ተግባር ሳይሆን በኢትዮጵያ ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ እየተሰራ ነው።
አገልግሎቱ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ከማድረግ ባሻገር የመረዳዳት እሴቶች በሕዝቡ ዘንድ እንዲጎለብቱ እያስቻለ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የሀገራችን ብልፅግና እንዲረጋገጥ እና የኢትዮጵያ ማንሰራራት እውን እንዲሆን እያገዘ ነው ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለፈው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቁጭት፣ በትብብርና በራስ ተነሳሽነት የተከናወነ በመሆኑም የላቀ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 35 ሚሊዮን ወጣቶችንና ሴቶችን በማሳተፍ 53 ሚሊዮን ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።
በተከናውኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም ከ86 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሀብት ማዳን መቻሉን አብራርተዋል።
ይኸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በብሔራዊ ደረጃ ወጥ የአሰራር ማዕቀፍ ተዘርግቶለት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የዋናው ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለስ አለሙ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያውያን ስንተባበር የማይፈታ ችግር እንደሌለ ማረጋገጫ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቋማትና ግለሰቦች በላቀ ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነትና ቅንጅት የሚፈፀም መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የበጎ ፈቃድ ስራ ወቅት ታይቶ የሚከወን ሳይሆን በማህበረሰባችን ውስጥ በዘላቂነት ባህል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎነት በመጪው ትውልድ ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎች ደግሞ ገንዘባቸውን ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በማዋጣት የሚሰሩት ተግባር በመሆኑ የኢትዮጵያውያን የቀደመ ጠንካራ የመረዳዳት ዕሴት መልሶ እንዲያንሰራራ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
በክልሉ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 656 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ በርካታ ወገኖችን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለጠ ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ በቅንጅትና በትብብር እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ከፌደራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አካላት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷል።