ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት የማጽናትና በተቀናጀ መልኩ ለልማት ምቹ መደላድል የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር)

ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት የማጽናትና በተቀናጀ መልኩ ለልማት ምቹ መደላድል የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

መምሪያው "ፅናት፤ ጀግንነትና ለዓላማ መስዋዕትነት የተቋማችን መገለጫዎች ናቸው" በሚል መሪ ሃሳብ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የዕውቅና መርሃ ግብር በባሕርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

‎‎በመርሃ ግብሩ ላይ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የፌዴራልና  የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


 

‎በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ‎የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ሰላቂ ሰላምና ልማትን የማረጋገጥ ጉዳይ በቅንጅትና በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎በተለይም የልማት ጸር እና የህዝብ ጠላት የሆነውን ፅንፈኛ ቡድን የጥፋት እንቅስቃሴ በመከታተል ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የጸጥታ ሃይል በቅንጅት ባከናወኑት ህግ የማስከበር ተግባር ጽንፈኛ ቡድኑ እየተበታተነ መሆኑን ገልጸው በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት የማጽናትና በተቀናጀ መልኩ ለልማት ምቹ መደላደል የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

‎የዛሬው እውቅና እና ሽልማትም ተልእኮና ግዴታቸውን በላቀ ሁኔታ ለፈፀሙ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የተበረከተ መሆኑን አንስተዋል። 

የዕውቅና እና ሽልማት የተሰጠው የማዕረግ ዕድገት፣ የደመወዝ እርከን፣ የትምህርትና ሌሎች የማበረታቻ ሽልማቶች መሆናቸውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም