ምክር ቤቱ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ለህዝቡ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በትብብር እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ለህዝቡ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በትብብር እየሰራ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ በመምከር ለህዝቡ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በትብብር እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ "ለዳበረ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ወሳኝ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ በወቅቱ እንዳሉት በሀገሪቱ እየታየ ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የድርሻውን እየተወጣ ነው።
''የሀሳብ ልዩነት የእርግማን ተምሳሌት የሆነበት ጊዜ አልፏል'' ያሉት ሰብሳቢው ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለህዝቡ ሰላምና ልማት በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስትም ምክር ቤቱን በአስፈላጊ ጉዳዮች ሁሉ እየደገፈ ስለመሆኑ አመልክተው በዚህም የተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት እየተገነባ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና ባህል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በክልሉ ቀደም ባሉት አመታት የዴሞክራሲ ስርዓት ባለመጎልበቱ የሀሳብ የበላይነት እንዲቀጭጭና የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው።
ችግሩን ለመፍታትም የለውጡ መንግስት የሀሳብ ነፃነት እንዲከበር በወሰደው ቁርጠኝነት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች መቋቋሙ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም ሀሳብን በሰለጠነ መንገድ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት ልዩነቶች በመነጋገር በመፈታታቸው ለክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማገዛቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ አንድ ላይ በመቆም ለህዝብ ሰላምና ልማት ላይ በትብብር መስራታቸውን አንስተዋል።
''የምንመራው ህዝብ አንድ ነው'' ያሉት አቶ ገብረመስቀል ''ሀሳባችንን ለህዝቡ አቅርበን በህዝቡ መዳኘት ባህላችን ሊሆን ይገባል'' ብለዋል።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫም በሰላምና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው ምክር ቤቱም የምርጫውን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በመድረኩም የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የጋራ ምክር ቤቱ ተወካዮች ተገኝተዋል።