ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ሚናችንን እንወጣለን -አባ ገዳዎችና የባህል ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ሚናችንን እንወጣለን -አባ ገዳዎችና የባህል ሽማግሌዎች
ዲላ ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ባህላዊ የሰላም እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ሚናቸውን እንደሚወጡ አባ ገዳዎች እና የባህል ሽማግሌዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አባ ገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች፤ ባህላዊ እሴቶቻችን የውስጥ አንድነታችን እና ህብረታችን ምንጭ በመሆናቸው የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ በህዝቦች የጸና ትስስርና አብሮነት እውን እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይ በባህላዊ የሰላም እሴቶች ግጭትን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ተከስቶ ሲገኝም የጋራ አሸናፊነትን ባረጋገጠ መልኩ መቋጨቱ ለዘላቂ የሰላም ግንባታ ተመራጭ ነው ብለዋል።
ይህንንም በተመለከተ የጉጂ አባ ገዳ ጃርሶ ዱጎ በሰጡት አስተያየት ገዳ ሰላም መሆኑን እና ስርዓቱም ለሰላምና አንድነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀሰት ወሬ እና በአሉባልታ ተታለው አለመግባባት ውስጥ የነበሩ ወገኖችን በገዳ የሰላም እሴት በመምከር ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው መመለስ መቻሉን በማሳያነት ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካቶች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሰላማዊ ኑሮ መጀመራቸውን አንስተው ይህም ተግባር ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ጌዴኦ በባህላዊ ስርዐቱ "ሰላምን እንሻማ" ይላል ይህም ከሰው ባለፈ ከተፈጥሮና ከፈጣሪ ጋር ጭምር ሰላም መሆኑን የሚያካትት ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ባህላዊ መሪ አባ ገዳ ቢፎሚ ዋቆ ናቸው።
ለህዝቦች ትስስርና ሰርቶ መለወጥ ሰላም መሰረታዊ መሆኑን አንስተው በእጃቸው ያለውን ባህላዊ እሴት በመጠቀም ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
የጋሞ የሀገር ሽማግሌ ሁዱጋ ሳዲቃ ሳፔ በበኩላቸው ባህላዊ የሰላም እሴቶች ግጭትን ቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ተከስቶ ሲገኝም የጋራ አሸናፊነትን ባረጋገጠ መልኩ መቋጨቱ ለዘላቂ የሰላም ግንባታ ተመራጭ ነው ብለዋል።
ለህዝብ ግንኙነት መሻከር ምንጭ የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ በህዝቦች የጸና ትስስርና አብሮነት እውን እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው ነባር ባህላዊ እሴቶች የህዝብን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
በተለይ ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምና ሀገረ መንግስት በመገንባት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በሀገር ደረጃ 72 ማህበረ ባህላዊ እሴቶችን በማስጠናት ለላቀ ሀገራዊ ሰላምና ማህበራዊ ልማት ለማዋል ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሰላም ሚኒስቴርና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር "ስለ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በዲላ ከተማ ማካሄዱ የሚታወስ ነው።