የተጠናከረ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የተጠናከረ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የተጠናከረ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
“የፋይናንስ ትምህርትን ማጎልበትና የደንበኞችን ጥበቃ ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ የፋይናንስ ዕውቀት ሳምንት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሀገራዊ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በመድረኩ ላይ እንዳሉት መንግስት የፋይናንስ ስርዓቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ሪፎርም በመተግበር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ እየሰራ ይገኛል።
እንደ ሀገር የፋይናንስ አስተዳደርና ቁጥጥር ሪፎርም መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ዘመናዊና ወጪ ቆጣቢ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት ዜጎች እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑንም አክለዋል።
በመሆኑም ለተጀመረው የዲጂታል ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማነት የፋይናንስ አገልግሎቱን በሁሉም መዋቅሮች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ተግባር እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
በክልሉ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ትግበራ መሰረታዊ ግቦችን ያሳካ ቢሆንም በውስጥ ኦዲት ትግበራ፣ በሰነድ ክምችትና በበጀት አጠቃቀም ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
ስለሆነም በክልሉ የተዘጋጀው የፋይናንስ ዕውቀት ሳምንት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሯ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ተወካይ ወይዘሮ ማርታ ኃይለማሪያም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎት ዕውቀትንና አካታችነትን በማሳደግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ ነው።
የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ግንዛቤ ማሳደግ ለፋይናንስ ዘርፉ አካታችነት፣ ጤናማነትና ደህንነት አዎንታዊ አበርክቶው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ።
ባንኩ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂን በመንደፍ የተገልጋዩን ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፋይናንስ እውቀት ሳምንት ዓላማም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮችንና ሌሎች ተገልጋዮችን ያማከለ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በይፋ በተጀመረው የፋይናንስ እውቀት ሳምንት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለመድረስ መታቀዱም ተመላክቷል፡፡